Job 13

1“ይህን ሁሉ ዐይኔ አይቷል፤
ጆሮዬም ሰምቶ አስተውያለሁ፤
2እናንተ የምታውቁትን፣ እኔም ዐውቃለሁ፤
ከእናንተ የማንስ አይደለሁም።
3ነገር ግን ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ፤
ከእግዚአብሔርም ጋር መዋቀሥ እሻለሁ።
4እናንተ ግን፣ በሐሰት የምትለብጡ ናችሁ፤
ሁላችሁ የማትረቡ ሐኪሞች ሆናችኋል።
5ምነው ዝም ብትሉ!
ያ ከጥበብ ይቈጠርላችሁ ነበር።
6እንግዲህ ክርክሬን ስሙ፤
የከንፈሬንም አቤቱታ አድምጡ።
7ለእግዚአብሔር ብላችሁ በክፋት ትናገራላችሁን?
ስለ እርሱስ በማታለል ታወራላችሁን?
8ለእርሱ ታደላላችሁን?
ለእግዚአብሔር ጥብቅና ልትቆሙ ነውን?
9እርሱ ቢመረምራችሁ መልካም ነገር ይገኝባችኋልን?
ሰውን እንደምታታልሉ፣ ልታታልሉት ትችላላችሁን?
10በስውር አድልዎ ብታደርጉ፣
በርግጥ እርሱ ይገሥጻችኋል።
11ግርማው አያስደነግጣችሁምን?
ክብሩስ አያስፈራችሁምን?
12ምሳሌዎቻችሁ የዐመድ ምሳሌዎች ናቸው፣
መከላከያችሁም የጭቃ ምሽግ ነው።

13“ዝም በሉ፤ እኔ ልናገር፤
የመጣው ይምጣብኝ።
14ሥጋዬን በጥርሴ፣
ሕይወቴንም በእጄ ለምን እይዛለሁ?
15ቢገድለኝም እንኳ በእርሱ ተስፋ አደርጋለሁ፤
ስለ መንገዴም ፊት ለፊት እከራከረዋለሁ።
ወይም በርግጥ እርሱ ይገድለኛል፤ ተስፋ የለኝም፤ ይሁን እንጂ

16ኀጢአተኛ በእርሱ ፊት መቅረብ ስለማይችል፣
ይህ ድፍረቴ ለመዳኔ ይሆናል።
17ቃሌን በጥንቃቄ አድምጡ፤
እኔ የምለውንም ጆሯችሁ በሚገባ ይስማ፤
18እንግዲህ ጕዳዬን ይዤ ቀርቤአለሁ፤
እንደሚፈርድልኝም ዐውቃለሁ።
19ሊከስሰኝ የሚችል አለ?
ካለም፣ ዝም ብዬ ሞቴን እጠብቃለሁ።

20“አምላክ ሆይ እነዚህን ሁለት ነገሮች ብቻ ስጠኝ፣
ያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፤
21እጅህን ከእኔ ላይ አንሣ፤
በግርማህም አታስፈራራኝ፤
22ከዚያ በኋላ ጥራኝ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤
ወይም እኔ ልናገር፤ አንተ መልስልኝ።
23በደሌና ኀጢአቴ ምን ያህል ነው?
መተላለፌንና ኀጢአቴን አስታውቀኝ።
24ፊትህን ለምን ትሰውራለህ?
እንደ ጠላትህስ ለምን ትቈጥረኛለህ?
25ነፋስ ያረገፈውን ቅጠል ታስጨንቃለህን?
የደረቀውንስ እብቅ ታሳድዳለህን?
26መራራ ነገር ትጽፍብኛለህ፤
የወጣትነቴንም ኀጢአት ታወርሰኛለህ።
27እግሬን በእግር ግንድ ታጣብቃለህ፤
ውስጥ እግሬም ላይ ምልክት አድርገህ፣
ዱካዬን አጥብቀህ ትከታተላለህ።

28“እንደ በሰበሰ ግንድ፣
ብል እንደ በላው ልብስ፣ ሕይወት እያደር ማለቅ ነው።
Copyright information for AmhNASV